የምግብ ጤንነትን መጠበቅ የሁሉም ባለድርሻ አካላትን ትኩረት ይፈልጋል ተባለ

“የኢትዮጵያ የምግብ ወለድ በሽታ ቅኝት” ፓዮኒር ፕሮጀክት ለባለድርሻ አካላት በፕሮጀክቱ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዎርክሾፕ አካሄደ።

የኢትዮጵያ የምግብ ወለድ በሽታ ቅኝት እንደ ሐገር ከተመረጡት ከሀረርጌ ፣ ከሰሜን ሸዋ ፣ ከቡታጅራ እና አርባ ምንጭ የጤናና የስነ_ሕዝብ ጤና ቅኝት ስርዓት ማዕከላት ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል።

“የኢትዮጵያ የምግብ ወለድ በሽታ ቅኝት” ፓዮኒር ፕሮጀክት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክቱ አባላት ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱት ባለሙያዎች ጋር በመተባበር የመጀመሪያ ዙር የግንዛቤ ማስጨበጫ ወርክሾፕ ሰሞኑን በደብረብርሀን ፣ በቡታጅራ እና አርባምንጭ ከተሞች አካሂዷል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ደሳለኝ አድማሱ “የኢትዮጵያ የምግብ ወለድ በሽታ ቅኝት” ፓዮኒር ፕሮጀክት አላማዉንና አተገባበሩ ምን እንደሚሆን በመድረኮቹ ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡ በስልጠናው ፕሮጀክቱ ከሚተገበርባቸው ከዞንና ከወረዳ ጤናና ግብርና ፣ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ፤ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ፤ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለሙያዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ጤና ባላሙያዎች ፣ የጤና ጣቢያ ሃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የጤናና የስነ_ሕዝብ ክትትል ስርዓት ባለሙያዎችና የማህበረሰብ ተወካዮች ተሳታፊ መደረጋቸው ፕሮጀክቱ የባለድርሻዎችን የነቃ ተሳትፎ ስለሚጠይቅ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር ውጤታማ ስራ ለማከናወን መሆኑን ኣብራርተዋል፡፡

ከተሳታፊዎች ጋር በተረደገው ዉይይት ምግብ “ከእርሻ እስከ ጉርሻ” ባለው ሂደት ደህንነቱ ካልተጠበቀ ጤናማ መሆን እንደማይችል የተገለጸ ሲሆን የምግብ ደህንነትን መጠበቅ የብዙ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ እና በምርምር ምክያቶቹን በመለየት የመከላከል ስራ መሰራት ስለሚያስፈልግ ፕሮጀክቱ ይህንን ለማሳካት ከባለድርሻዎች ጋር እንደሚሰራ ዶክተር ደሳለኝ አብራርተዋል።

የፕሮጀክቱ ምክትል አስተባባሪ ዶክተር ተስፋዬ ጎበና እና የፕሮጀክቱ አባል ዶ/ር መርጋ ዴሬሳ ለባለድርሻ አካላትና የማህበረሰብ ተወካዮች የምግብ ወለድ በሽታ ምንነት ፣ መንስኤ ፣ አስከፊነትና ክትትልን እንዲሁም የበሽታው ስርጭትና በማህበረሰቡና በሃገር ኢኮኖሚ ላይ ያለዉን ተጽእኖ በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥተዋል።

የምግብ ወለድ በሽታ ክትትል ፕሮጀክት በሚኖረው የአራት ዓመት የስራ ቆይታ የምግብ ወለድ በሽታ መንስኤዎችን በምርምር በመለየት ፣ መፍትሔዎችን በመጠቆም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በመረጃ የተደገፉ የውሳኔ ሀሳቦችን እንደሚያቀርብ የፕሮጀክቱ ምክትል አስተባባሪ ዶክተር ተስፋዬ ጎበና ጨምረው አብራርተዋል።

“ምግብ ከእርሻ እስከ ጉርሻ ባለው ሂደት ደህንነቱ ካልተጠበቀ ጤናማ መሆን አይችልም” ያሉት በስልጠናው ላይ የተሳተፉት የደብረብርሐን ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ሐላፊ አቶ በቀለ ገብሬ የምግብ ደህንነትን መጠበቅ የብዙ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።

የምግብ መበከል በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩትም በግምት ሳይሆን በምርምር መንስኤውን በመለየት የመከላከል ስራ መሰራት እንዳለበት አቶ በቀለ አብራርተው ከስልጠናው የተገኘውን ግንዛቤ ወደ ተግባር እንዲቀየር እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

የሰሜን ሽዋ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ ጸዳለ ሰሙንጉስ ደብረ ብርሃን ከተማ ላይ ፣ የጋሞ ዞን ም/ጤና መምሪያ ሃላፊ ባንጌ ባንጃ አርባ ምንጭ ከተማ ላይ ፣ የምስራቅ ጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ ሰለሞን ጉግሳ ቡታጅራ ላይ በተካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ ዎርክሾፕ ላይ በመገኘት የምግብ ወለድ በሽታ ስርጭት ሰፊ በመሆኑ በማህበረሰቡ ዉስጥ ያለውን ይህን የጤና ችግር ለመቅረፍ ፕሮጀክቱ በተገቢው ጊዜ የመጣና ችግር ፈቺ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በደብረ ብርሀን ፣ ቡታጅራና አርባምንጭ ከተሞች የተሰጠው ስልጠና ላይ ከተሳታፊዎች በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በምግብ ምክንያት የሚከሰቱ ህመሞችን ለመከላከል የምግብ ግብአቶችን ከማምረት እስከ መመገብ ድረስ ባሉ ሂደቶች ውስጥ ተሳትፎ ያላቸውን አካላት ትብብር ስለሚጠይቅ ለምግብ ደህንነት መጠበቅ ሁሉም የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *